ለማያውቁት አላማ ከመዋጋት መማረካቸው ጀግንነት ነው

ለማያውቁት አላማ ከመዋጋት መማረካቸው ጀግንነት ነው

በጣም ልብ ይሰብራል እጅግ ያሳዝናል እነዚህ ኢትዮጵያውያን በማያውቁት ጦርነት ይሳተፋሉ ላልገባቸው አላማ ይሞታሉ። አለቆቻቸው እና ባለስልጣናቱ በነሱ ሞት ላይ ሆነው ቤተሰባቸውን ይመራሉ በሞቀ አልጋ እየተኙ በሳል ከጥሬ አማርጠው እየበሉ በየቀኑ ሀሴት ያደርጋሉ። ለእኔ እነዚህ ጀግኖች ናቸው እጅ መስጠታቸው መማረካቸው ከጀግናም በላይ ጀግና ያደርጋቸዋል ምክንያቱም በማያውቁት ጉዳይ ስላልሞቱ።

እነዚህ ወጣቶች ለወላጆቻቸው ልጆች ናቸው። ለሚስታቸው ባል ናቸው ልጅ ካላቸው ለልጆቻቸው አባት ናቸው ታዲያ ለማን ብለው ይሙቱ? አሁን ኢትዮጵያ ላይ ያለው ጦርነት ወንድም ወንድሙን ገሎ ከመፎከር ውጪ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንዳችም ትርፍ የለውም። ታዲያ ይህ ነዳጅ የማይገኝበት ወርቅ የማይቆፈርበት አልማዝ የማይወጣበት ለሀገርም ሆነ ለዜጋ አንዳች ጥቅም በሌለው ጦርነት ለምን ይሞታል። በውጪ ሀገር ተቀምጠው በፌስቡክ እና በዩቱብ ጀግናው መከላከያችን የሚሉ ሁሉ በግል ተዋጋ ብትሏቸው አይደፍሩትም ግን ድሀውን ያስጨርሳሉ።

በመከላከያ ውስጥ ያላችሁ አሊያም በመከላከያ ውስጥ ለማያውቁት ጦርነት የሚሞቱ ቤተሰብ ያላችሁ ቤተሰቦቻችሁን አንቁ በከንቱ አይሙቱባችሁ። ሀገር በሌላ ጠላት ሀገር ተወራ እያለ ነገር ግን ልጆቻችሁ ወንድሞቻችሁ ቤተሰባችሁ እየሞቱ ያሉት ምንም ትርፍ በሌለው ጦርነት ላይ ነው። እነዚህ ምስኪን ኢትዮጵያውያን ለኢሳያስ የበቀል ጥም መጠቀሚያ ሲሆኑ ለአብይ አህመድ ደግሞ የስልጣን ማረዘሚያ ማገዶዎች ናቸው። ህዝቤ ሆይ ንቃ ከዚህ ሁሉ እልቂት እና ውድመት በኋላ አንድ ቀን ድርድር ወይ እርቅ የሚባል ነገር መብጣቱ አይቀረም። ደግሞም ይመጣል።

ታዲያ ይህ ሁሉ ወጣት ከሞተ ከቆሰለ ከተሰቃየ በኋላ እርቅ ወይም ድርድር አሊያም ደግሞ ዘላለም የማያልቅ ጦርነት ከሆነ አይቆጭም? ይቆጫል። በኢትዮ – ኤርትራ ጦርነት ሺህ ወጣቶች አልቀዋል። ቤተሰብ ተበትኗል ምንም ትርፍ ግን አልነበረውም። ይህው አሁን ታረቅን ታዲያ የሞቱት አይቆጭም ይቆጫል። ዛሬም እየሆነ ያለው ይሄው ነው የሚያልቅ ያልቃል የሚሰደድ ይሰደዳል በመጨረሻም የአለም ሰላም አስከባሪ ይገባል ከዛ እርቅ ወይም ድርድር ይኖራል። አለቀ። አሁንም ቢሆን አልረፈደም በማያውቁት ጦርነት የሚሞቱትን ኢትዮጵያውያን ልናነቃቸው ይገባል። በሁለቱም ወገን። ሞት ለማንም አይጠቅምም። በድጋሚ እነዚህ የተማረኩት ውድ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ክብር ትልቅ የጀግንነት ጀብዱ ሰርተዋል። ክብር ይገባቸዋል። ያለ አላማ አልሞቱም።

About Author