ገድሎታል

ገድሎታል

አስታውሳለሁ ከዛሬ 10 አመት በፊት ካናዳ የመጣሁ ሰሞን የነጮቹ ትህትና ፤ ፍቅር አሰጣጥ ቅንነታቸው ግርም ይለኝ ነበር።

ታዲያ አንድ ቀን ይህ ሁኔታቸው ስላስገረመኝ ኢትዮጵያ የማውቀው ፓስተር ስለ ካናዳ ሲጠይቀኝ በጣም ደስ ብሎኝ ስለ ነጮች ባህሪ አወራው ነበር።

ይህ ፓስተር ዝም ብሎ እየሰማኝ በውስጡ ግን በፍርሀት ሆኖ በኢየሱስ ስም እያለ ቀስ ብሎ ድምፅ እያወጣ የሚፀልይ ይመስላል።

ሳወራ ባህሪያቸው አስደስቶኝ ቅንነታቸው ገርሞኝ አኗኗራቸው አስቀንቶኝ በአድናቆት ተሞልቼ የመጣልኝን አወራው ነበር።

አድናቆቴ ስለበዛበት ነው መሰለኝ ፓስተሩ አቋረጠኝ። ተስፍሽ ለመሆኑ ግን ትፀልያለህ? አለኝ። እኔም አዎ አልኩት።

ወዲያው በደንብ ፀልይ አምልኮተ ነጭ ውስጥ እየገባህ ነው!ነጮች ከዲያቢሎስ በላይ አደገኛ ናቸው አለኝ።

እኔም የማየውን ቅንነት እንዴት ከዲያቢሎስ ጋር ታወዳድረዋለህ? አልኩት።

ነጭ ነፃ ስጦታ የለውም! ሲያደርግልህም ፤ ሲወድህም፤ ሲጠላህም ከጀርባው አንድ ነገር አለው።

የነጭ ባህሪ ማለት የውሸት እየሳቁ የእውነት ይገሉሀል አለኝ። እኔ በአይኔ የማየውን ቅንነት እንዴት በዚህን መጠን ክፋታቸውን ያወራል አልኩኝ።

ከ 5 አመትበኋላ ግን ለአገልግሎት አሜሪካ መጥቶ ቀረ። አሜሪካ ፕሮሰሱ ስላልተቀበሉት በቦርደር በኩል ካናዳ ገባ።

ሲገባ የተቀበሉት ነጭ የቀይመስቀል ሰራተኞች ነጭ ፖሊሶች በእንክብካቤ ነበር።

ወደ መጠለያ አስገቡት ቁርስ ፤ ምሳ ፤ እራት እያበሉ 1 ክፍል ቤት ሰጥተው ከምግብ ውጪ በየወሩ ከ 1200 ዶላር በላይ እየሰጡ

በነፃ እያስተማሩት ከ 80 ሺህ ዶላር በላይ የሚፈጀውን የቲዮሎጂ ትምህርትም በነፃ አስተምረውት አስመረቁት።

ካናዳ ከመጣ በኋላ በስልክ አግኝቶ ስለ ነጮች መልካምነት ያኔ የነገርኩትን አሁን ለእኔው ቃል በቃል ይነግረኝ ጀመር።

እኔም ፓስተር ግን ትፀልያልህ? አልኩት ከት ብሎ ስቆ ይህ ሁሉ ነገር እኮ የፀሎቴ መልስ ነው በምጠላቸው በኩል ፀሎቴ ተመለሰ አለኝ።

ዛሬ ለንደን ኦንታሪዎ የምትባል ከተማ ላይ ነጭ አግብቶ በእርሻ እና በዶሮ ርባታ ላይ ተሰማርቶ እየኖረ ነው።

አንዳንዴ በስልክ ያገኘኛል ይሄን ሲያነብ ምን ይሰማው ይሆን።

ለማንኛውም ነጭ ብለን የምናስባቸው ሰዎች ልክ እንደኛው ሰው ናቸው።

ግን የእውነት ከልባቸው ቅኖች ናቸው። ሰውን የሚያዩት በሰውነቱ ብቻ ነው። ይህ ማለት ግን ክፉ ነጮች የሉም ማለት አይደለም።

በቁምህ አስለቅሰው ያለምንም ፍንጭ ሊገሉህም ይችላሉ።

ብዙ ጊዜ ነጭ ፖሊስ ጥቁርን ገደለው! የሚል ዜና ተደጋግሞ በአሜሪካ ይነገራል።

የጆርጅ ፍሎይ ትልቁ ምሳሌ ነው! ቅንነታቸው ግን ከዚህም በላይ ነው! ገደለው ስንል በፍቅርም

ገደለው ያስብላል። ይህ ፎቶ በፍቅር ሲገለው የሚያሳይ ነው። ፍቅር የሚሰጥበትን መንገድ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ እያስለቀሰ በፍቅሩ ገሎታል።

About Author