ቁማሩ ደርቷል

ቁማሩ ደርቷል

ህዝቤ ይግባውም አይግባውም የቁማሩ ታዳሚ ሆኖ አንዱ በሌላው ጎን ቆሞ በልተናል ሲል ሌላኛው ተበልተናል እያለ በህዝብ ላይ ይቆምራል።

መንግስትም ቁማሩ ተመችቶት አጫዋቿን ሀገር አንዴ እጅሽን አንሺ አንዴ ደግሞ እጅሽን ጫኚ እያለ የቁማሩን ጫወታ በእጥፍ አሙቆታል።

መንግስት ሲፈልግ ጎረምሶች እያለ ቁማር አጫዋች አሜሪካኖችን ሲዘልፍ አጨብጫቢው ህዝብ አብሮ ወሮበላ አሜሪካ ብሎ ይጮሀል።

የናንተን ስንዴ አንፈልግም ነቀዝ የበላው ነው ሲል የመንግስት ሹመኛ ህዝቡ አሜን እኛ በቀኝ ያልተገዛን ሲበላ የኖረውን ስንዴ ነቀዝ ብሎ ይሳደባል።

ብቻ ምን አለፋችሁ ቁማር መሆኑን የምታውቁት እኛ የማንም ጣልቃ ገብነት አያስፈልገንም ያለው መንግስት መልሶ ሞግዚት ይፈልጋል።

የቁማሩ ታዳሚ ያልገባው ህዝብ ድንገት ተነስቶ እኛ ነጭ አምላኪ አይደለንም በነጭ አምልኮ አንያዝም ሲል ሁሉም ተነስቶ ነጭ አምላኪ እያለ ይሳደባል።

ነጭ ሀገር አቋርጦ ሲመጣ ደግሞ እኛ እንግዳ ተቀባይ የ ሶስት ሺህ አመት ታሪክ ያለን ህዝቦች በማለት አንድን ነጭ ተስፋ በማድረግ ሀገር ምድሩ ያወራል።

ነጭ ፊቱን ሲያዞርብን ደግሞ ኢትዮጵያ የቃልኪዳን ሀገር ነች የማንም እርዳታ አያስፈልጋትም እንላለን። በጓሮ በኩል ዞረን እረ እባካችሁ ምነው ዝም አላችሁ እንላለን።

ይህው ዛሬ ሌላ አዲስ የቁማር አጫዋች በጓሮ በር ሲጠራ በፊት ለፊት በር ሰተት ብሎ ቤተመንግስት ድረስ ገብቶ ቁማሩን እየቆመረላችሁ ነው።

ገራሚው የቁማር ሂደት በኢትዮጵያ ላይ መአቀብ ሲጣል ዝም ያለው የቁማሩ ተጫዋች ልክ መአቀቡ ሲፀና በዚህ መልኩ ብቅ አለ።

ከአሜሪካ ምንም ነገር አንፈልግም በራሳችን አድገን በራሳችን ተለውጠን የእድገት ማማ ላይ እንደርሳለን ያለው መንግስት አሁን ምን ፈልጎ እልል አለ?

ትላንትና ቻይናን እና ሩሲያን ሲያሞካሽ ያደረው ህዝብ አሁን ደግሞ አንዱን የአሜሪካ ሴናተር የአመቱ አመትባል አስመስሎት ሽር ብትን እያለ ይገኛል።

እኔ ግን የማዝነው ኑሮው ፈቀቅ የማይለው የኢትዮጵያ ህዝብ እና ምንም የማያውቀው የቁማሩ አካል የሆነው ከርታታው ህዝቤ ነው።

የሄደውም የመጣውም የሚመጣውም እንደፈለገ ይጋልበዋል። በአጉል ተስፋ ወጥሮ ያሰቃየዋል። ይዝቤም ይህ ሳይገባው በባዶ ይጮሀል። አዝናለሁ።

About Author